ባለስልጣኑ ከመመሪያ ውጭ ለፈጸሙ አራት የግል ት/ቤቶች ውሳኔውን ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ባለስልጣን ዋና ስራአስኪያጅ እንዳስታወቁት የኢ.ፊ.ድ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር በአለም አቀፍ ብሎም በአገራችን በተከሰተው የኮሮና ወረርሽን ምክንያት ከመጋቢት 7/2012 ዓ.ም ጀምሮ ት/ቤቶች እንዲዘጉ መወሰኑ ይታወቃል፡፡  የተቋረጠው መደበኛ ትምህርት እስኪጀመር ድረስ  ተግባራዊ የሚሆን ውሳኔም አስቀምጧል፡፡ይህን አገራዊ ችግር በትብብርና በመደጋገፍ ለመሻገር አብዛኛው የትምህርት ተቋማት በመመሪያው መሰረት ተግባራዊ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

p1 2

ባለስልጣኑ በመጀመሪያ ዙር ባደረገው ምልከታ 21 የትምህርት ተቋማት በውሳኔው መሰረት የትምህርት አገልግሎት ክፍያን ከመመሪያ ውጭ  በመጠየቃቸው በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ማስተካከያ አድርገው ሪፖርት ለባለስልጣኑ እንዲያደርጉ በደብዳቤ እንዳሳወቃቸውና ከነዚህም ውስጥ 17 የትምህርት ተቋማት ማስተካከያ በማድረግ ሪፖርት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ቀሪዎቹ አራት የትምህርት ተቋማት ግን ከመመሪያ ውጭ ወላጆችን ተገቢ ያልሆነ ክፍያ በመጠየቃቸው ለ2013 ዓ.ም የመማር ማስተማር ተግባር ማከናወን እንደማይችሉ ባለስልጣኑ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

እነዚህም ት/ቤቶች በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ለምለም ት/ቤት እና ሮማን ት/ቤት

በየካ ክፍለ ከተማ ስሪ ኤም አካዳሚ እንዲሁም

በአራዳ ክፍለ ከተማ ገነት መሰረተ ክርስቶስ ት/ቤት መሆናቸው ታውቋል፡፡